የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት
Addis Ababa Abattoirs Enterprise

መጪውን የፋሲካ በዓል ቅድመ ዝግጅትን በማስመልከት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር እንዲሁም የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር በጋራ በመሆን በዛሬው ዕለት ለግል እና ለመንግስት የሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ!

ሚያዚያ 04 ቀን 2015 ዓ.ም

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ስራአስኪያጅ አቶ ሰኢድ እንድሪስ እንደገለፁት የትንሳኤ በዓል በተቋሙ ከፍተኛ እርድ ከሚከናወንበት እና ሰፊ የስራ እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት ወቅት በመሆኑ ተቋሙ በሰው ሃይል ፣ በግብዓት እንዲሁም የእርድ ክፍሎችን እና ተሸከርካሪዎችን እድሳት እና ጥገናዎችን በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተከናውኗል በማለት ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የሰው ኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ድርጅቱ ከ ቋሚ ሰራተኞች በተጨማሪ ከ 250 በላይ ዜያዊ ሰራተኞች መቅጠሩን እና ለኅብረተሰቡ ንፅህናውን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በፍጥነት እና በቅልጥፍና ለማቅረብ ከ 43 በላይ የስጋ መጓጓዣ ተሸከርካሪዎች ዝግጁ መሆናቸውን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ 2 ሺህ 5 መቶ በላይ ትላልቅ እንስሳት እና ከ 2 እስከ 3 ሺህ በግ እና ፍየል የእንስሳት ዕርድ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል በማለት በ ዘጠኝ ወራት ዉስጥ ተቋሙ ከእርድ ፣ ከተረፈ ምርቶች ፣ ቆዳና ሌጦ እና ሌሎች ገቢዎች ከ 3 መቶ 67 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ዋና ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል።

በድርጅቱ በር ላይ በሚገኙት ሱቆች የበግና የፍየል ስጋ በኪሎ ግራም 400 መቶ ብር እንዲሁም የበሬ ስጋ በኪሎ ግራም 500 መቶ ብር እንደሚሸጥ በመግለፅ ድርጅቱ በሱቆቹ የሚሸጡ ስጋዎችን ጥራት የመቆጣጠር እና ዋጋ የመተመን ሃላፊነቱን በመውሰድ ሱቆቹን በኪራይ በዘርፉ ለተሰማሩ ነጋዴዎች በመስጠት አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል በማለት ህብረተሰቡ ከበዓሉ እለት ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል አቶ ሰዒድ እንድሪስ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በተከታታይ የሚከበሩ በዓላት መቃረባቸዉን ተከትሎ የዘጠኝ ቀናት የዘመቻ ስራ ማከናወኑን የባለሥልጣኑ ም/ል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትግስት በዳዳ ተናግረዋል።በልኳንዳ ቤቶች ላይ ቁጥጥር አድርጎ ከደረጃ በታች የሆኑ የዛገ ብረት ያለባቸዉ የስጋ መሸጫ ሱቆች እንዲታደሱ ፣ የንጽህና ጉድለት ያለባቸዉ መደብሮች ጽዳታቸዉን እንዲያሻሽሉ ፣ የሰራተኛ ጤና ምርመራ የማያከናዉኑ እና የምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ሳያሟሉ በስራ ላይ የነበሩ መገኘታቸዉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የቃል ማስጠንቀቂያ ለ 4 ሺህ 5 መቶ 55 ተቋማት የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ 6 መቶ 98 ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በሌላ በኩል ባለስልጣኑ በስምንት ተቋማት ላይ የማሸግ እርምጃ የወሰደ ሲሆን በአንድ ተቋም ላይ የህግ ተጠያቂነትን ለማሰጠት በሂደት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር እንዲሁም የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር በበኩላቸው ለትንሳኤ በዓል በቂ የቁም እንስሳት ከክልሎች ወደ መዲናዋ የገቡበት ሁኔታ ስላለ ከነገ ጀምሮ የልኳዋንዳ ቤት ነጋዴዎችም ሆኑ ህብረተሰቡ ግብይት መፈፀም እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ ቀለም ወርቅ የገለፁ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች በተመመጣጣኝ ዋጋ በቂ የስጋ አቅርቦት ስለሚኖር ህብረተሰቡ ከበዓሉ እለት ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ጨምረው ተነግረዋል።

ዲዛይን እና የተገነባው በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት