የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት
Addis Ababa Abattoirs Enterprise

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ሀላፊዎች በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በመገኘት የካይዘን ትግበራ ላይ ጉብኝ አካሄዱ!!

መጋቢት 26፤ቀን 2015 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በከተማ አስተዳደሩ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ዘርፍ ስር የሚገኝ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ እና በተቋሙ የሚስተዋለውን የተደራሽነት ችግር፣ የደንበኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ አለመሆን፣ የሠራተኛው ተነሳሽነት ማነስ፣ የአካባቢ ብክለት መጨመር አሳሳቢና ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ በመሆኑ በ2013 ዓ.ም በተቋሙ ስራ አመራር ቦርድ እና በማኔጅመንቱ ውሳኔ መሠረት የካይዘን ትግበራ ወደ ስራ እንዲገባ በማድረግ አመርቂ ውጤት አምጥቷል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ የቢሮው ሀላፊዎች፣የካይዘን ዘርፍ ዳይሬክቶሬት እና ባለሙያዎች በድርጅቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በመገኘት በካይዘን ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ላይ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በተቋሙ የተጀመረው የካይዘን ስራ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እና የተተገበሩ ስራዎችን መነሻ በማድረግ ሌሎች ተቋማት ተሞክሮ በመውሰድ ሰፊ የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ የስራ ጉብኝት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ገልፀዋል፡፡

በተቋሙ የካይዘን ትግበራ በመከናወኑ ምርትንና ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከመኖሩም በላይ የካይዘን ትግበራን በማከናወን ድርጅቱን ካላስፈላጊ ወጪ በማዳን ጥቅም ላይ ሊውሉ ያልቻሉ ግብአቶችን ወደ ገንዘብ እንዲለወጡ በማድረግ ተቋሙ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ መደረጉ ድርጅቱ ካይዘንን በአግባቡ በመተግበሩ የተገኘ ውጤት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰኢድ እንድሪስ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ካይዘን አተገባበርን በተመለከተ ሌሎች ተቋማት ከቄራዎች ድርጅት ሰፊ ልምድ እንደሚወስዱ እምነቴ ነው በማለት የተሰሩ ስራዎች ቀጣይነት ኖሯቸው እንዲከናወኑ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ድጋፍና ክትትል በማጠናከር ለወደፊትም ውጤታማ ስራዎችን በጋራ እናከናውናል ሲሉ ክብርት ሀቢባ ሲራጅ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ዲዛይን እና የተገነባው በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት